1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእጥፍ የጨመረው የአውሮጳ ሀገራት የጦር መሣሪያ ግዥ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3 2016

ባለፉት አምስት ዓመታት የአውሮጳ ሀገራት የጦር መሣሪያ ግዢ በእጅጉ ጨምሯል። በአውሮጳ የጦር መሣሪያ ክምችት የጨመረበት አንዱ ምክንያት የዩክሬን ጦርነት ቢሆንም ሌላው ምክንያት ደግሞ የአውሮጳ ሀገራት ራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉት ዝግጅት ነው። በጦር መሣሪያ ሽያጭ ፈረንሳይ አሁን ሩስያን ተክታ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ትገኛለች።

https://p.dw.com/p/4dRg2
USA weiter an der Spitze bei Waffenexporten/F-35
ምስል picture alliance/dpa/dpa-Zentralbild

በአውሮጳ በእጥፍ የጨመረው የጦር መሣሪያ ግዥ


ባለፉት አምስት ዓመታት የአውሮጳ ሀገራት የጦር መሣሪያ ግዢ በእጅጉ መጨመሩን ትናንት ይፋ የተደረገው ዘገባ አስታውቋል። የመስኩ ተመራማሪዎች እንዳሉት በነዚህ ዓመታት በአውሮጳ ሀገራት የጦር መሣሪያ ግዥው ያደገው በከፊል በዮክሬኑ ጦርነት ምክንያት ነው።ይህም የዩናይትድ ስቴትስ ጦር መሳሪያ አምራቾችን ዋነኛ ተጠቃሚ አድርጓል።  እንደ ሲፕሪ ዘገባ ዩክሬን አሁን በብዛት የጦር መሣሪያ በማስገባት ከዓለም አራተኛውን ደረጃ ይዛለች። በሲፕሪ ጥናት መሠረት የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ከዛሬ ሁለት ዓመት ወዲህ ቢያንስ 30 የአውሮጳ ሀገራት ለዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ የጦር መሣሪያዎችን በወታደራዊ እርዳታ ሰጥተዋል። በአውሮጳ የጦር መሣሪያ ክምችት የጨመረበት አንዱ ምክንያት የዩክሬን ጦርነት ቢሆንም ሌላው ምክንያት ደግሞ የአውሮጳ ሀገራት  ራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉት ዝግጅት ነው ሲሉ ዶቼቬለ በሲፕሪ ዘገባ ላይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ተናግረዋል። 

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የጦር መሣሪያ በብዛት ወደ ሀገርዋ የምታስገባው ዩክሬን ብቻ አይደለችም።ሌሎች የአውሮጳ ሀገራትም የጦር መሣሪያ ግዢያቸውን አሳድገዋል። አብዛኛዎቹ የጦር መሣሪያዎች የሚመጡት ደግሞ ከዋነኛዋ የዓለም የጦር መሣሪያ አምራች ከዩናይትድ ስቴትስ ነው። በሲፕሪ ጥናት መሠረት ከጎርጎሮሳዊው 2019 እስከ 2023 ዓም ባሉት ጊዜያት ወደ አውሮጳ ከገባው ጦር መሣሪያ 55 በመቶው ከዩናይትድ ስቴትስ ነው የተገዛው። ከዚያ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት ግን አሜሪካን ለአውሮጳ ሀገራት የሸጠችው የጦር መሣሪያ መጠን ከሌሎች ሀገራት ከገዙት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ነበር ።

ቀይ ባህር ላይ የተሰማራው የዩናይትድ ስቴትስ የውጊያ መርከብ
ቀይ ባህር ላይ የተሰማራው የዩናይትድ ስቴትስ የውጊያ መርከብ ምስል Ruskin Naval/U.S. Navy/AP Photo/picture alliance

የሲፕሪ ዘገባ እንደሚያሳየው ከዚህ ቀደም በጦር መሣሪያ ሽያጭ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ሩስያ ወደ ውጭ የምትልከው የጦር መሣሪያ መጠን በግማሽ ቀንሷል የሲፕሪን ዘገባ ከጻፉት አንዱ ፒተር ቬሰማን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የሩስያን የጦር መሣሪያዎች ዋነኛ ደንበኛ የነበሩት ህንድና ቻይና እንደቀድሞ ከሩስያ በብዛት መግዛት ማቆማቸው አንዱ ምክንያት ነው።ቻይናም ሆነች ህንድ አሁን የጦር መሣሪያ አምራቾች ስለሆኑ ለሩስያ ገበያ መቀዝቀዝ ምክንያት ነው ተብሏል። በተለይ ህንድ በቴክኒክና በከፊልም በፖለቲካዊ ምክንያቶች የፈረንሳይ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም የእስራኤልን የጦር መሣሪያዎች ነው የምትገዛው ።ከዚህ ሌላ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ሀገራት ከሩስያ የጦር መሣሪያ እንዳይገዙ በአንዳንድ ሀገሮች ላይ ተጽእኖ ማድረጋቸውም ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።ዓለም፤ በኮሮና ቀዉስ ዉስጥ ወታደራዊ ወጭዋ ጨምሮአል


«ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ሀገራት በተወሰነ ደረጃ ከዚህ ቀደም የሩስያ የጦር መሣሪያ ደንበኛ በነበሩ ሀገራት ላይ ጫና ያደርጋሉ። ይህ በተለይ በግብጽ ላይ ጎላ ብሎ ማየት የቻልነው ነው። ግብጽ ከሩስያ የውጊያ ጀቶችን ልትገዛ የነበረ ቢሆንም ይህን እንዳታደርግ በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገባት ጫና ምክንያት አሁን የተራቀቁ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ከፈረንሳይ ልትገዛ ነው። »
የጦር መሣሪያ ሽያጭ ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ዩናይትድ ስቴትስ ናት። አሁን በጦር መሣሪያ ሽያጭ ፈረንሳይ ሩስያን ተክታ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ትገኛለች።  ፒተር ቬሰማን ለዶቼቬለ እንዳስረዱት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈረንሳይ በርካታ ደንበኞችን ማግኘቷ በጦር መሣሪያው ንግድ ከፍተኛው ቦታ እንድትይዝ አድርጓታል። 

F-22 የዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ አውሮፕላን
F-22 የዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ አውሮፕላንምስል Ben Bloker/US Air Force/dpa/picture alliance

«እንደሚመስለኝ የዚህ መልስ በብዛት ፈረንሳይ ከምታራምደው ስልታዊ የሉዓላዊነት ፖሊስ ጋር የተያያዘ ነው።በመሠረቱ ፈረንሳይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሌላ አካል የጦር መሣሪያ ጥገኛ ሳትሆን የራስዋን ወታደራዊ ኅይል መጠቀም ነው የምትፈልገው። ለዚህ ደግሞ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ ያስፈልጋታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የጦር መሣሪያ መሸጥ አለባት። ያ ካልሆነ ብዙ ወጪ የሚያስወጣት ይሆናል። በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት ራፋል የተባለ ተዋጊ አውሮፕላኗና ሌሎች ባህር ሰርጓጅና የጦር መርከቦቿ ብዙ ደንበኞች በማግኘታቸው የጦር መሣሪያ ንግዱ ተሳክቶላታል። »የአፍሪቃ ወታደራዊ ወጪ እና የሲፕሪ ዘገባ
ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚሉት ከሩስያ ዩክሬን ጦርነት ወዲህ አውሮጳውያን ከዩናይትድ ስቴትስ በብዛት የጦር መሣሪያ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በየሀገራቸውም የጦር መሳሪያዎችን በብዛት እያመረቱ ነው። በጀርመንም በመከላከያው ዘርፍ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ይታሰቡ ያልነበሩ ለውጦች እየተደረጉ ነው። ጀርመን አሁን እንደቀድሞው በጦር መሣሪያ ሽያጭ ከዓለም አምስተኛው ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው።ዋነኞቹ ደንበኞቿም የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ናቸው። የሲፕሪው ቬሰማን እንዳሉት 2023 ዓም ለጀርመን የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በጣም ጥሩ ዓመት ነበር። «2023 በጀርመን የጦር መሣሪያ ሽያጭ ትልቅ እምርታ የታየበት ዓመት ነው። ዓመቱ በከፊል ሀገሪቱ ለዩክሬን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርዳታ የሰጠችበት ዓመት ከመሆኑ ጋር ለሲንጋፖር ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለእሥራኤልና ለግብጽ ደግሞ ትላልቅና አነስተኛ የጦር መርከቦችን የሸጠችበት ዓመት በመሆኑ ነው» 

የጀርመን ሊፓርድ 2 ታንኮች
የጀርመን ሊፓርድ 2 ታንኮች ምስል Fabian Bimmer/REUTERS

የሩስያ ዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲያበቃ የድርድር ሀሳቦች ቢቀርቡም ሰሚ አላገኙም። በቅርቡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ያቀረቡት የድርድር ጥሪም በጎ ምላሽ አላገኘም ።ዶክተር ለማ እንደሚሉት ድርድር የአውሮጳ ሀገራት ባላጋራቸውን ለመቋቋም የሚያስችል የጦር መሳሪያ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ዝግጅት ጥረት ነው።

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር