1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለ ስቅለትና የትንሳኤ ገበያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2016

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ስነስርዓት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በድምቀት ታውሶ ዋለ፡፡ በዓሉ አዲስ አበባ መንበረ ፓትሪያርክ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ታላላቅ የሃማኖቱ አባቶች እና ምዕመናን በተገኙበት በልዩ ድምቀት ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4fUIZ
በዓለ ስቅለት በአዲስ አበባ
በዓለ ስቅለት በአዲስ አበባ ምስል Seyoum Getu/DW

በዓለ ስቅለትና የትንሳኤ ገበያ

በዓለ ስቅለትና የትንሳኤ ገበያ

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ስነስርዓት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በድምቀት ታውሶ ዋለ፡፡ በዓሉ አዲስ አበባ መንበረ ፓትሪያርክ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ታላላቅ የሃማኖቱ አባቶች እና ምዕመናን በተገኙበት በልዩ ድምቀት ተከብሯል፡፡ የፊታችን እሁድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል ምክኒያት በማድረግ በአዲስ አበባ ለበዓሉ ማድመቂያ የሚውል ገበያም ደርቷል፡፡

የስነስቅለት መንፈሳዊ ትርጉም

የትንሳኤ በዓል መዳረሻ የሆነው የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በልዩ ትኩረትና ስነስርዓት ከሚከበሩ አበይት በዓላት ተጠቃሽ ነው፡፡ መምህር ይቅርባይ እንዳለ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመሪ እቅድ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡ ዛሬ ስከበር የዋለው የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚከበረው የቤተክርስቲያኗ በሆነው ልዩ ስነስርዓት ነው ይላሉ፡፡ “ጠዋት ተይዞ ወደ ሃና እና ቀያፋ የተመላለሰበት ነው፡፡ ሶሰርት ሰዓት መያዙን ስድስት ሰዓት መሰቀሉን፤ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በመስቀል ላይ መቆየቱን እንዲሁም ከመጽሃፍ ቅዱስ በወሰደችው መሰረት ክርስቶች ስሰቀል ጸሃይ መጨለሟ ጨረቃ ደም መልበሷ እንዲሁም ከዋክብት መርገፉ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በልዩ ስርዓት ይዘከራል፡፡ እያንዳንዱ ነገር በምሳሌ ይከወናል፡፡ እሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የደም ላብ እንዳላበው ምዕመናን በስግደት ላባቸውን እየጠረጉ እየደከሙ እየሰገዱ ያንን ዘክራሉ የበረከቱም ተቋዳሽ ይሆናሉ” ብለዋል፡፡

የፋሲካ በዓል መዳረሻ የቀንድ ከብት ገበያ
የፋሲካ በዓል መዳረሻ የቀንድ ከብት ገበያ ምስል Seyoum Getu/DW

የምዕመናን ተሳትፎ

ዛሬ በዓሉ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማሪያም ገዳም ሲከበር ቁጥራቸው እጅግ የላቀ ምዕመናን በስፍራው ተገኝተው የስግደትና ጸሎት መርሃግብሮቹን ተካፍለዋል፡፡ ታዳሚ ምዕመናኑም እለቱን ልዩ በበማለት ይገልጹአታል፡፡ “ክርስቶስ የተሰቀለውን ነገር እያሰብን የምናደርገው ነገር ሁሉ ደስ ይላል” የሚሉት ምዕመናኑ እለቱ የይቅርታ እና የመተሳሰብ ብሎም ሁሉም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ያዳነበትን ልዩ ፍቅር በማሰብ የሚያልፍ በማለት ለስርዓቱ የሚሰጡትን ትርጉም ያስረዳሉ፡፡

የትንሳኤ ግብይት

በሌላ በኩል የፊታችን እሁድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል ምክኒያት በማድረግ በአዲስ አበባ እንደወትሮው የበዓል ገበያውም ደርቷል፡፡ በተለይም የዋጋ ጭማሪ ተስተውሎበታል በተባለው የአንስሳት ግብይት በርካታ ከብቶች ከአገሪቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ገብተዋል፡፡ አቶ አዕምሮ የተባሉ የበግ ግዢ እየፈጸሙ ያገኘናቸው ሸማች ዋጋውን እንደውም እንደገመቱት ከፍተኛ አለመሆኑን አስረድተው አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡ “እኔ እንዳውም ማለት ሁላችንም በዚህ ገቢያ መንገድም ብዙ ቦታ ችግር ስላለ በታም ወደዳል ሚል ግምት ነበረን፡፡ ግን ምንም አይልም ደህና ነው” በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ጌትዬ በለጡ ደግሞ ከሰሜን ሸዋ መሃል ሜዳ ጌራ መድር በጎች እና ፍየሎችን ይዘው ለገቢው ብቅ ብለዋል፡፡ “እኔ የያዝኳቸው አነስ ያሉና መካከለኛ የሚባሉ በጎች እንዲሁም ፍየሎች ነው፡፡ አነስተኛ በጎች ከስድስት ሺህ ጀምሮ አሉ፡፡ ግን ደህና በግ እስከ 20 ሺህ ይገኛል፡፡ፍየልም እንዲሁ 25 ሺኅ ድረስ ይሸጣል” ነው ያሉት፡፡ ተገኝ ያዘው ደግሞ የሰንጋ ነጋዴ ሲሆኑ በካራአሎ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ “ከሀረር፣ መንዝ፣ ቦረና፣ ጅሩ ትልልቅ የሚባሉ ሰንጋዎች በደንብ ገብተዋል፡፡ አነስተኛ 65 ሺህ ሲሆን እስከ 200 ሺህ ትልቅ የሚባለው ሰንጋ ይገኛል፡፡ ከገና ግን በአንድ በሬ ላይ እስከ 20 ሺኅ ያህል ጭማሪ ታይቷል” ነው ያሉት፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ