1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጣና ሐይቅ ህገወጥ ዓሳ ማስገር የደቀነዉ አደጋ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2015

ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው መሆኑን የጣና ሐይቅ አካባቢ ነዋሪዎችና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡ ያልተፈቀዱ የዓሳ ማስገሪያ መሳሪያዎችን መጠቀምና ወቅቱን ያልጠበቀ ማስገር ዋናዎቹ የችግሩ ምንጮች ናቸውም ተብሏል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ከ5000 በላይ አስጋሪዎች እንዳሉ የአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4OdvB
Äthiopien See Tana Illegale Fischerei Biniyam Hailu
አቶ ቢኒያም ኃይሉ በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባህር ዳር  ዓሳና ሌሎች ውሀ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል አስተባባሪና ተመራማሪ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው ነው

ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው መሆኑን የጣና ሐይቅ አካባቢ ነዋሪዎችና ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፣ ያልተፈቀዱ የዓሳ ማስገሪያ መሳሪያዎችን መጠቀምና  ወቅቱን ያልጠበቀ  ማስገር ዋናዎቹ የችግሩ ምንጮች ናቸውም ተብሏል፣ የዓሳ ምርምር ጣቢያዎችና ባለሙያዎች ደግሞ ሀብቱ የሚያገግምበትን ሁኔታ እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፣ በጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ከ5000 በላይ አስጋሪዎች እንዳሉ የአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡

Äthiopien See Tana Illegale Fischerei
በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደዉ ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው ነዉ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የህገወጥ ዓሳ ማስገር በጣና ሐይቅና በሌሎችም የውሀ አካላት ውስጥ ለሚገኘው የዓሳ ምርት መጠን መቀነስ ምክንያት እንደሆነ በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባህር ዳር  ዓሳና ሌሎች ውሀ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ሀብት፣ አያያዝና አጠቃቀም ኬዝ ቲም አስተባባሪና ተመራማሪ አቶ ቢኒያም ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ከምክንያቶቹ ዋና ያሉትንም አስቀምጠዋል፡፡ “የጣና ሐይቅ ዓሳ ከዓመት ወደ ዓመት ምርቱ እየቀነሰ ነው፣ ምርቱ ከቀነሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ህገወጥ ዓሳ ማስገር ነው፣ አስጋሪዎች እየተጠቀሙበት ያለው የማሽን መረብ የሚባለው ነው፣ ይህ መረብ የሚመረተው ግብፅ አገር ሆኖ በሱዳን በኩል በህገወጥ መንገድ ይገባል፣ አስጋሪዎች መረቡን በህገወጥ ካገኙት በኋላ ቀዳዳዉ እጅግ ጠባብ በመሆኑ ለምግብነት ያልደረሱ ጫጩት ዓሳዎችን ጨምሮ ይይዛቸዋል፣ ለምርቱ መቀነስ ይህ አንዱ ምክንያት ነው፡፡”

የአካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ አቤል ጫኔም ህገወጥ መረብና ሌሎች ምክንቶች ለምርቱ መቀነስ ምክንያት መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ “ከዓሳ አስጋሪዎች ጋር ሰፊ የሥራ ግንኙነት አለኝ፣ የሐይቁንም ብዝሐ ህይወት በደንብ አውቀዋለሁ፣ አሁን ያለውንም ሆነ ቀድሞ የነበረውን የዓሳ ሀብት መጠን አውቀዋለሁ፣ ከዚህ በፊት የነበረው የማስገሪያ መረብ 10 ሴንቲ ሜትር ነበር የሚያዘው የዓሳ መጠንም 500 ግራም ነበር፣ዛሬ ግን የመረቡ ቀዳዳ መጠን ቀንሷል የሚሰገረው ዓሳው መጠንም ወደ ጫጩትነት ወርዷል፣ በማይሰገርበት ወቅትና ቦታ ይሰገራል፣ ልቅ የሆነ የማስገር ስራ ስላለ ቀስበቀስ የዓሳ ምርት እየቀነሰ መጥቷል፡፡”

እየተመናመነ የመጣውን የዓሳ ምርት እንዲያገግም ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ደግሞ ተመራማሪው አቶ ቢኒያም አመልክተዋል፡፡ “ምርቱ እንዲጨምር ለማድረግ በሰው ሰራሽ ዘዴ የተፈጥሮ የመራቢያ ዘዴ ባለመጠበቅ ወንድና ሴት ዓሳዎችን ከሐይቁ በመያዝ፣ በቤተ ሙከራ በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል እያራባን ወደ ሐይቁ እየመለስን ነው፡፡ ሌሎች የውሐ አካላትምየዓሳ ምርታቸው በሚመናመንበት ጊዜ በተመሳሳይ መንገድ የማራባት ስራዎች ይከናወናሉ፣ ሌላው ደግሞ አስጋሪዎች ግንዛቢያቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ ህገወጥ መረብ እንዳይ|ጠቀሙ፣ በመራቢያ ወቅትና በመራቢያ ቦታዎች ማስገር እንዳይደረግ ትምህርት ይሰጣል፣ ህጋዊ የማስገሪያ መረብ እንዲጠቀሙም ትምህርት ይሰጣል” ብለዋል፡፡

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ አቤልም 3ሺህ600 ካሬ የሀይቁን ክፍል ከልለው በራሳቸው ተነሳሽነት ከ70ሲህ  እስከ 80 ሺህ ዓሳ በየዓመቱ በማራባት ወደ ሀይቁ እንዲለቀቁ እያደረጉ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien See Tana Illegale Fischerei
በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደዉ ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው ነዉ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

“የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ሐይቁ ወደነበረበት የዓሳ ምርታማነት ፕሮጀክት ቀርጨ እየሰራሁ ነው፡፡ 3600 ካሬ ቦታ ወስጂ አንድ የዓሳ ማገገሚያ ቦታ አዘጋጅቻለሁ፣ በዓመት ከ70ሺኅ እስከ 80ሺህ ዓሳ በማራባት ወደ ሐይቁ እጨምራለሁ፡፡” የዓሳ ተመራማሪው አቶ ቢኒያም በህገወጥ መንገድ የሚያሰግሩ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ቢኖርም ተግባራዊ ባለመሆኑ ህገወጥነቱን መቀነስ አልተቻለም ይላሉ፡፡

በአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የዓሳ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ አበበ ፋንታሁን በበኩላቸው ህጉ በሁሉም አካላት እኩል እየተተገበረ ባለመሆኑ በቅርቡ የጋራ ውይይት እንደሚደረግና ህጉ በህገወጦች ላይ ተግባራዊ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

“የዓሳ አስተዳደር ኮሚቴ እስከ ቀበሌ ድረስ ተዋቅሯል፣ ሆኖም ሁሉም ኮሚቴ ተግባሩን በእኩል እያከናወነ አይደለም፣ አንዳንዱ በትክክል ተግባሩን ያከናውናል፣ ሌለው ደግሞ የሚጠበቅበትን እየሰራ አይደለም፣ ይህ ግብረሓይል ተጠናክሮ ወጥ ሆነ ሥራ እንዲሰራ ለማድረግ በቅርቡ የጋራ ውይይት ይደረጋል፣ ህገወጥነትንም ይከላከላል፡፡” አቶ አበበ የዓሳ ምርት ቀንሷል የሚለውን ስሞታ አይቀበሉም፣ ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

Äthiopien See Tana Illegale Fischerei Abel Chane
የጣና ሐይቅ አካባቢ ነዋሪ አቶ አቤል ጫኔምስል Alemenew Mekonnen/DW

“ከምርት አኳያ ስናየው አስጋሪው ምርት ቀንሷል የሚል ስሞታ ያቀርባል፣ ችግሩ ግን የአስጋሪው ቁጥር መጨመር ነው ቀደም ሲል ጥቂት አስጋሪ ነው የነበረው፣ አሁን ጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ሙሉ ህይወቱን በማስገር ላይ ያለ 5000 አስጋሪ አሉ፣ አጠቃላይ ምርት ግን ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው የመጣው፣ ምክንያቱ ደግሞ ሐይቆቹን፣ ኩሬዎችን ወንዞችን ግድቦችን ማስፋፋት በመቻላችንና የዓሳ መራባያ ማድረግ በመቻሉ ነው፣ ከዚህ በፊት ሐየቆች ብቻ ነበሩ የዓሳ መራቢያዎች የዓሳ ዓመታዊ ፍጆታም ወደ 0.5 ደርሷል፣ ከዚህ በፊት ከዚህ በታች ነበር፣ አሁን የትኛው ቦታ፣ የትኛውም ዞን የዓሳ ምርት አለ፣ በፊት ጣና ሐይቅ ዙሪያና ደቡብ ወሎ አካባቢ ብቻ ነበር፡፡ ”

Äthiopien See Tana Illegale Fischerei
በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደዉ ህገወጥ የዓሳ ማስገር ሀብቱን እያመናመነው ነዉ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በዓመት  ከ30 እስከ 40 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት ማምረት የሚያስችሉ የውሀ አካላት ቢኖሩም እስካሁን እየተመረተ ያለው ግን ከ22 ሺህ ቶን እንደማይበልጥ ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለምነዉ መኮንን

አዜብ ታደሰ