1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የውህደት ውይይት አልጀመርኩም» ህወሓት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

ከብልፅግና ጋር የሚያገናኘው የጋራ አጀንዳው የፕሪቶርያው ውል መሆኑን የገለጸው ህወሓት ውሉ በሙሉ እንዲተገበር አጋዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብልፅግና ፓርቲና ህወሓት በመቐለና አዲስአበባ መወያየታቸውን አስታውቋል። ከዚህ ውጭ ህወሓትና ብልፅግና ፓርቲ በመገናኛ ብዙሐን እንደተባለው የጀመሩት ወደ ውህደት የሚመራ ውይይት የለም ሲል አስተባብሏል።

https://p.dw.com/p/4f8hw
Äthiopien | Eyasu Tesfay  Mitglied von TPLF
ምስል Million Haileyessus/DW

«ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የውህደት ውይይት አልጀመርኩም» ህወሓት

ከህዝብ ተደብቆ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የሚደረግ ውህደት የለም ሲል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ገለፀ። ህወሓት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ ንግግር ጀመረ ተብሎ መገለፁ ህወሓት አስተባብሏል። ለዶቼቬለ የተናገሩት የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ እያሱ ተስፋይ ከሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና ጋር የተጀመረ የውህደት ውይይት የለም ሲሉ የገለፁ ሲሆን የተሰራጨው መረጃም ከእውነት የራቀ ብለውታል።የብልጽግናና የህወሓት ባለሥልጣናት ዉይይት

ለዶቼቬለ የተናገሩት በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ፅሕፈት ቤት የፓርቲው ፕሮፖጋንዳ ዘርፍ ሐላፊ አቶ እያሱ ተስፋይ ህወሓት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የሚያገናኘው እና የጋራ አጀንዳው የፕሪቶርያው ውል ነው ያሉ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር አጋዥ በሆኑ ጉዳዮች ብልፅግና ፓርቲ እና ህወሓት በመቐለ እና አዲስአበባ መወያየታቸው ገልፀዋል። የብልጽግና እና የህወሓት ልዩነት እንዴት ከረረ?ከዚህ ውጭ ህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ በመገናኛ ብዙሐን እንደተባለው የጀመሩት ወደ ውህደት የሚመራ ውይይት የለም ሲሉ አስተባብለዋል።ህወሓት እና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ብልፅግና መሰረታዊ የዓላማ ልዩነት አላቸው ያሉት የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር አቶ እያሱ ተስፋይ ይህ ባለበት አሁን ይሁን ቀጣይ የሚዋሃዱበት ሁኔታ የለም ሲሉ አክለዋል።

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባንዲራ
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባንዲራ ምስል Million Haileyessus/DW

 "ህወሓት የራሱ ዲስፒሊን ያለው ህዝባዊ ድርጅት ነው፥ ተደብቆ የሚያደርገው ነገር የለም" ያሉት የህወሓቱ አመራር፥ እስካሁን በተደረጉ ግንኙነቶች ውህደት አጀንዳ ያደረገ ውይይት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር እንዳልተደረገ ተናግረዋል።"ከህወሓት ጋር ተደራደሩ ማለት ስህተት ነው" ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
ሌላው ያነጋገርናቸው የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ በበኩላቸው፥ ግጭት ላይ የነበሩት የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ህወሓት እና የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና ወደ ውይይት መመለሳቸው በራሱ ለዘላቂ ሰላም ትልቅ ትርጉም ያለው በማለት ይገልፁታል። እንደ የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ገለፃ ሁለቱ ፓርቲዎች ሊወያዩባቸው የሚችሉ በርካታ አጀንዳዎች አሉ።
የህወሓት እና ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በያዝነው ወር ሁለት ግዜ በመቐለ እና አዲስአበባ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። በተነገረው የውህደት አጀንዳ ዙርያ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከብልፅግና ፓርቲ በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ