1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዚያ 16፣2016 የዓለም ዜና

Negash Mohammedረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

ባለፈው ሳምንት በሰነድ ማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡---አዲስ አበባ ዉስጥ የሁለት ቤተሰብ አባላት በሚኖሩበት ቤት ላይ ዛሬ ማለዳ የተናደ ድንጋይና አፈር 7 ሰዎች ገደለ።---ጎርፍ ሰሞኑን ኬንያ ዉስጥ 32፣ ታንዛኒ 58 ሰዎች ሲገድል ቡሩንዲ ዉስጥ ከ100 ሺሕ በላይ ሕዝብ አፈናቅሏል።-----ዓለም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የምትመራበት ሕግና ሥርዓት ከጥፋት አፋፍ ላይ መድረሱን አምንስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4f9Lk

አዲስ አበባ-የቀሲስ በላይ የክስ ሂደት

ባለፈው ሳምንት  በሰነድ ማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀሲስ በላይ መኮንንን ጨምሮ፤ ያሬድ ፍስሃ እና ዳባ ገናና በተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ላይ የፖሊስ ምርመራ ስራዎችን ተመልክቷል፡፡

ፖሊስ  ቀረኝ ያላቸውን ምርመራዎች ለማድረግ  የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።የቀሲስ በላይ ጠበቆች ባንፃሩ ቀሲስ በላይ እጅ የሚገኝ አሊያም ከሳቸው ጋር የተያዘ ምንም አይነት ሰነድ አለመኖሩንና በሌሎች ሰዎች መታለላቸውን ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን ከጠበቆቻቸው አንዱ አቶ ዮናታን ዘውዴ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ቀሲስ በላይ የሃይማኖት አባትና ቋሚ አድራሻ ያላቸው በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠበቆቻቸዉ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ 8 ቀን ብቻ በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮውን ለሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.ሰጥቷል፡፡ ጠበቃ ዮናታን ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን የዋስትና መብት ውድቅ ሲያደርግ ዝርዝር ምክኒያት ሳይሰጥ ለፖሊስ ተጨማሪ ቀናት መፍቀዱን ገልጸዋል፡፡ቀሲስ በላይ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብና ከአፍሪካ ኅብረት ኦፊሳላዊ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ የተለያዩ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በከሳቸው ተገልጾ ነበር፡፡ዘገባዉን የላከልን የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጉቱ ነዉ።

 

አዲስ አበባ-ቤት ተደርምሶ 7 ሰዉ ሞተ 

አዲስ አበባ ዉስጥ  አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በተለምዶ ጠሮ መስጊድ በሚባል አካባቢ ዛሬ ማለዳ ለግንባታ የተከማቸ አፈርና ድንጋይ አንድ ቤት ላይ ተደርምሶ ሰባት ሰዎች ሞቱ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበዉ ለቤት ግንባታ የተከመረዉ ድንጋይና አፈር ባልታወቀ ምክንያት ከመሬት እየወጣ ካለው ግንባታ ጋር ተደርምሶ ባለ ሶስት ክፍሉን መኖሪያ ቤት ጨፍልቆታል።ቤቱ ዉስጥ ተኝተዉ የነበሩ የሁለት ቤተሰብ 7 አባላት በሙሉ ሞተዋል።ሟቾቹ ከ4 ዓመት እስከ 30 ዓመት የእድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ነበሩ።የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት ኮሚሽናቸው ህይወት ለማዳን ቢሞክርም አልተሳካለትም።ከሟቾች ጎረቤቶች አንዱ አቶ አሊ አማን ጎረቤት በሌሊቱ ተነስቶ የደረሱት የድንጋይ መደርመስ ከፍተኛ ድምጽ በመስማት ነው ብለዋል፡፡ፖሊስ የአደጋዉን ትክክለኛ መንስዔ እያጣራ መሆኑን አቶ ንጋቱ ማሞ አስታዉቀዋል።

ለንደን-የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አመታዊ ዘገባ

 

የሠብአዊ መብቶች ጥበቃ ከብዙ አስርታት ዓመታት ወዲሕ በመላዉ ዓለም ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠበት አምንስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ዛሬ ባወጣዉ ዓመታዊ ዘገባዉ እንዳለዉ ጋዛ፣ ዩክሬንና «ተጠናክረዋል» ያላቸዉ የፈላጭ ቆራጮች መንግስታት ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና  ሠብአዊ መብቶችን በመጣስ የዓለምን ሥርዓት እያናጉት ነዉ።የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ እንደሚሉት ባለፉት 6 ወራት ጋዛ ዉስጥ የደረሰዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከየትኛዉም ጊዜና አካባቢ የከፋ ነዉ።
                                   
«የመዘገብነዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ደረጃ ከምንጊዜዉም በላይ አቻ የለዉም።ጋዛ ዉስጥ ባለፉት 6 ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሠላማዊዉ ሰዎች ሰለባ መሆናቸዉን፣ረሐብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን፣ሠላማዊ ፍልስጤሞችን በጅምላ መቅጣትን፣ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ጋዜጠኞች መግደላቸዉን፣ከፍተኛ ቁጥር  ያላቸዉ የሰብአዊ ጉዳይ ሠራተኞች መገደላቸዉን አይተናል።በሰላማዊ ሰዎች ላይ እስካሁን ከተመዘገበዉ ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ጉዳት ደርሷል።»
እስራኤል በጋዛ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ ወደር የሌለዉ ጉዳት ከማድረስ አልፋ እርምጃዋን ተገቢ እንደሆነ አድርጋ ማቅረቧንና ዩናይትድ ስቴትስም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የእስራኤልን እርምጃና አቋም መደገፏን የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አስታዉቀዋል።ዋና ፀሐፊዋ አክለዉም ሩሲያም ዩክሬን ዉስጥ ተመሳሳይ ግፍ ማድረሷን ገልጠዋል።
                             
«ዩክሬን ዉስጥም ሩሲያ ተመሳሳይ ቅርፅ ያለዉ የመብት ጥሰት ማድረሷን አይተናል።» 
አምንስቲ ኢንተርናሽናል ከጋዛና ዩክሬን በተጨማሪ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ምያንማር፣ ኢራንና አፍቃኒስታንን በመሳሰሉ ሐገራት ከፍተኛ የመብት ጥሰት መድረሱን  ዘግቧል።የብሪታንያ መንግስት ሕገ-ወጥ የሚላቸዉን ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ ለማጋዝ መወሰኑንና አዲስ ያስፀደቀዉን ደንብም መንበሩን እዚያዉ ለንደን ያደረገዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ተቃዉሞታል።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ እንዳሉት ባለፈዉ 12 ወራት የታየዉ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጥሰቱን ለማስቆም መንግስታት አለመጣራቸዉ ዓለም ከ2ኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የምትከተለዉን ሥርዓት ከጥፋት አፋፍ አድርሶታል።

 

ናይሮቢ-የኬንያ ፖሊስ 118 ሰዎችን ያለፍርድ ዉሳኔ ገደለ-የሰብአዊ መብት ድርጅቶች

የኬንያ ፀጥታ አስከባሪዎች ባለፈዉ የጎርጎሪያኑ ዓመት 2023፣ 118 ሰዎችን ያለፍድ ቤት ትዕዛዝ መግደላቸዉን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታወቁ።ሑዩማን ራይትስ ዋች፣ አምንስቲ ኢንርናሽናልና የጠፉ ድምፆች የሚባለዉ የኬንያ የመብት ተሟጋች ድርጅት በጋራ እንዳስታወቁት ከግማሽ የሚበልጡት ሰዎች የተገደሉት «ወንጀልን ለመከላከል» በተወሰደ እርምጃ ነዉ።45ቱ የተገደሉት ደግሞ የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከአምና መጋቢት እስከ ኃምሌ የተጠሩትን የተቃዉሞ ሰልፍ ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት ርምጃ ነዉ።የሶስቱ ድርጅቶች ዘገባ እንዳመለከተዉ 10 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።ኬንያ ዉስጥ በ2023 ከፍርድ ቤት ዉሳኔ ዉጪ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በ2022 ከተገደሉት በ12 ቀንሷል።

 

ናይሮቢ-ጎርፍ መንገዶችን አጥለቀለቀ ሰዎችን አፈናቀለ

የኬንያ ርዕሰ ከተማ የናይሮቢ አዉራ መንገደች ዛሬ ደራሽ ጎርፍ ወደሚወርድበት ወንዝነት ተለዉጠዉ አረፈዱ።በተከታታይ የጣለዉ ዝንብ ያስከተለዉ ጎርፍ አዉራ ጎዳኖችን፣ ድልድዮችን፣ ቤቶችንና መኪኖችን በዉኃና ጭቃ ሞልቶ የከፊል ከተማይቱን እንቅስቃሴ አዉኮታል።ሰሞኑን ምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ የጣለዉ ከባድ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ ታንዛኒያ ዉስጥ 58 ፣ኬንያ ዉስጥ 32 ሰዎች ወስዷል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ጎርፉ ብሩንዲ ዉስጥ ከ100 ሺሕ በላይ  ኬንያ 40 ሺሕ፣ ታንዛኒያ ዉስጥ ደግሞ በ10 ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅሏል።ኤል ኚኖ የሚባለዉ የዓየር ንብረት መዛባት ምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ በጎርፍና ድርቅ በየዓመቱ በርካታ ሕዝብ ይገድላል፤ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ያፈናቅላል።አምና ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና  ኬንያን ባጥለቀለቀዉ ጎርፍ 300 ሰዎች ሞተዋል።በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል። 

 

እየሩሳሌም-የእስራኤል ጦር ራፋን እንደሚወር አስታወቀ

የእስራኤል ጦር በሕዝብ የተጨናነቀችዉን የደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ከተማ ራፋሕን ለመዉረር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።ለወትሮዉ ወደ 150 ሺሕ የሚገመት ሕዝብ የሚኖርባት ራፋሕ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲሕ ከተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች የተፈናቃለ አንድ ሚሊዮን ያክል ተጨማሪ ሕዝብ ሠፍሮባታል ተብሎ ይገመታል።የእስራኤል ጦር ራፋሕን ከወረረ እስካሁን ካለቀዉ ፍልስጤማዊ የበለጠ ሕዝብ ያልቃል ብለዉ የሰጉ ወገኖች እስራኤል ጦር ራፋህን እንዳይወር እየተማፀኑ ነዉ።ሮይተር ዜና አገልግሎች የእስራኤል ጦር አዛዦችን ጠቅሶ ዛሬ እንደዘገበዉ ግን ጦሩ ራፋሕን ለመዉረር ዝግጅቱን አጠናቅቆ የመንግስት ባለስልጣናትን ዉሳኔ እየጠበቀ ነዉ።የፍልስጤም ባለስልጣናት እንደሚሉት እስራኤል ከመስከረም 26 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ላይ በከፈተችዉ ጥቃት ከ34 ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅታለች።እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ 1ሺ200 ሰዎች መግደሉና ከ130 ያክል እንዳገተ መሆኑን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።

 

በርሊን-የጀርመን  ኩባንዮች እንዲጠነቀቁ የሥለላዉ ድርጅት አሳሰበ

የጀርመን ኩባንዮች ቻይናን ከመሳሰሉ ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት ጋር ሲዋዋሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የጀርመን የሐገር ዉስጥ ሥለላ ድርጅት አሳሰበ።በጀርመንኛ ምህፃሩ BfV ተብሎ የሚጠራዉ የስለላ ድርጅት ምክትል ፕሬዝደንት ዚናን ዜሌን ዛሬ እንዳሉት የቀረጥና መሰል የኮምፒዉተር ፕሮግራሞችን  አሳልፎ መስጠት ቻይኖች የሰጪዉን ኩባንያ ሚስጥሮች በቀላሉ እንዲያገኙ ይረዳል።ዜሌን የጀርመን ኩባንያና የንግድ ተቋማት ኃላፊዎችን ያስጠነቀቁት፣ የጀርመን ሕግ አስከባሪዎች ለቻይና ይሰልሉ ነበር የተባሉ 4 ሰዎች መያዛቸዉን ካስታወቁ ከዕለታት በኋላ መሆኑ ነዉ።የቻይና ጆሮ ጠቢ ተብለዉ ከተያዙት አንዱ በአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት የጀርመን ቀኝ ፅንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲ (AFD) እንደራሴ የማክሲሚሊያን ክራሕ ረዳት ነዉ።የፖለቲከኛዉ ረዳት በሰላይነት ተጠርጥሮ መያዙን  የጀርመን ባለሥልጣናት «አሳሳቢ» እያሉት ነዉ።መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስን ዛሬ እንዳሉት ወንጀለኞች ለፍርድ ይቀርባሉ። 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።