1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 25.05.2024 የዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2016

https://p.dw.com/p/4fUZ3

በአማራ ክልል ከፌዴራሉ መንግስት ጋር እየተዋጉ የሚገኙት የታጣቂው ቡድን ፋኖ መሪዎች የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር «የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ » ነው ሲሉ ከሰሱ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በጦርነቱ ወቅት በአማራ ኃያሎች ቁጥጥር ስር ወደ ገቡ አካባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ማቀዱን እንደማይታገሱ የታጣቂ ቡድኑን አመራር ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ከጎንደር አካባቢ የተወከሉ እና የታጣቂ ቡድኑ አመራር አባል መሆናቸው የተነገረላቸው አቶ በየነ አልማው  በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰጡት በተባለው መግለጫ «የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመብን ነው ፤ በኃይል የሚደረግ የትኛውንም መስፋፋት አንታገስምም» ብለዋል።

 የታጣቂዎቹ መግለጫ የተሰማው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እስከ የፊታችን የሰኔ ወር መጀመሪያ ድረስ ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ በተያዘው ዕቅድ ላይ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው። ጄኔራል ታደሰ ወረደ በመግለጫቸው  የክልሉ ባለስልጣናት ተፈናቃዮችን በመመለስ ዕቅዱ ላይ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

ሮይተርስ የጠቀሳቸዉ የፋኖ መሪዎች በትናንቱ መግለጫቸው ከወደ ትግራይ የተሰማው ዕቅድ «ጠብ አጫሪነት » ነው ፤ብለዋል።የፌዴራል መንግስቱ በትግራይ ክልል ባለስልጣናትም ሆነ በታጣቂ ቡድኑ ለተሰጠው መግለጫ መልስ አለመስጠቱን ዘገባው አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገበኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ህዝበ ውሳኔ እንደሚደረግባቸው ከዚሕ ቀደም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ አስታዉቀዉ ነበር።

 

ከሚያዝያ 2016 ዓ ም አጋማሽ ጀምሮ በራያ አላማጣና አካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክያንት ተፈናቅለው ከነበሩት የአላማጣ አካባቢ ነዋሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገለጸ። 
የራያ አማራ የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት «አካባቢውን ለቅቆ መሄድ የበለጠ የማንነትና የወሰን ጥያቄን ለአደጋ የሚያጋልጥ » በመሆኑ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል፡፡
«እየተመለሰ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፤ በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። ቦታው ቤቱን ለቆ እየሄደ ፣ እየመጣ በሄደ ቁጥር ከሌላ አቅጣጫም የሚገባ ኃይል ስለሚኖር በስደት ሆኖ ሃብቱንም ንብረቱንም ከሚያጣ እዚያው በቤቱ ላይ ሆኖ ቢሞት ይሻላል በሚል ህዝቡጋ መረዳዳት አድርገን ወደ አካባቢው የተመለሰበት ሁኔታ ነው ያለው። ሁለተኛው ፖለቲካዊ ትርጉምም አለው። ህዝቡ እየተሰደደ በሄደ ቁጥር የሚደረገው ህዝበ ውሳኔ እድሉን ለሌላ መክፈት ነው የሚሆነው »
ተፈናቃዮች  በመጠለያ ጣቢያ መቆየት ለተለያዩ ወረርሽኖች ስለሚያጋልጥ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ካደረጉ ምክንያቶች ተጠቃሽ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል፣ ነገር ግን “የትግራይ ታጣቂዎች ሰሞኑን ከያዟቸው አካባቢዎች እየወጡ ነው” እየተባለ ስለሚነገረው ጉዳይ ግን ምንም መረጃ እንደሌላቸው አቶ ኃይሉ ገልጠዋል፡፡
መምህር እንደሆኑ የነገሩን ተመላሽ የአላማጣ ከተማ ተፈናቃይ ከተፈቀደላቸው የፀጥታ ሰዎች ውጭ በከተማው ሌሎች ታጣቂዎች ባለመኖራቸው በሰላም ቤታቸው ገብተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«በመከራ አሳልፈናል። ከዚያ በኋላ በሳምንቱ ማለት ነው በመኪና ወደ ዋጃ ካምፕ እንድንመለስ ከተደረገ በኋላ ሰው በዋጃ ካምፕ ምንም የሚቀርብ ነገር ምንም የሚጠይቅ ሰው ስለጠፋ የተወሰነ የደፈረው ለጊዜው ገብቶ ያው ራሱን በቤቱ ቢሞትም እንኳ በቤቱ መሆን እንዳለበት አስቦ ነው»
በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ከራያ አላማጣ፣ ከራያ ባላ፣ ከወፍላና ከአላማጣ ከተማ አስተዳደር ወደ 39 ሺህ ተፈናቃዮችን መመዝገቡን የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በወቅቱ አሳውቆ ነበር። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ደግሞ የተፈናቃዮቹን ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ ያደርሰዋል፡፡ 
 

 

ኬንያ እና ታንዛንያ የጎርፍ መጥለቅለቅ የሚያስከትል ዝናብ ይጥላል በሚል ሥጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ከግድቦች እና ሌሎች ተጋላጭ አካባቢዎች  ለቀው እንዲወጡ አሳሰቡ።

በሁለቱ ሃገራት በዚህ ሳምንት ከ350 በላይ ሰዎች ህልፈት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ካፈናቀለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በኋላ ሌላ የከፋ አደጋ እንዳይከሰት ዜጎቻቸውን እያስጠነቀቁ ነው።«በባህር ዳርቻ አካባቢዎች የሚነሳ እና ኃይለኛ ዝናብ ሊያስከትል የሚችል ሳይክሎን ሂዳያ የተሰኘ ብርቱ ማዕበል እንቅስቃሴ በህንድ ውቅያኖስ ላይ መታየቱን » የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጽ/ቤት አስታውቋል። ኬንያ ካለፈው የመጋቢት ወር አንስቶ 188 ዜጎቿን በጎርፍ መጥለቅለቅ ስትነጠቅ ፤ ከ90 በላይ ሰዎች አሁንም ድረስ የደረሱበት አልታወቀም ። በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ብርቱ ስጋት ካሳደረው ብርቱ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊደርስባቸው ይችላል ተብለው ከተለዩት ውስጥ መዲናዪቱ ናይሮቢ እንደምትገኝበት የሜትርዎሎጂ መረጃዎችን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በተመሳሳይ 155 ዜጎቿን በጎርፍ መጥለቅለቅ የተነጠቀችው ታንዛንያም የሳይክሎን ሂዳያ አውሎ ናፋስ የሚያስከትለው ብርቱ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ስጋት ይዟታል። ዜጎቿም ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ባለስልጣናት እየወተወቱ ነው።

 

ሩስያ በጀርመን ላይ «ትፈፅመዋለች» ያሉትን የሳይበር ጥቃቶች ሀገራቸው « በፍጹም እንደማትታገስ» የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ አስጠነቀቁ ። 

ባለፈው የጎርጎርሳውያኑ 2023 በጀርመን የጥምር መንግስት ውስጥ በገዢው ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ላይ ተቃጥቶ ከነበረው የሳይበር ጥቃት ጀርባ የሩስያ መንግስት መረጃ መንታፊዎች መኖራቸውን ቤርቦክ አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አናሌና ቤርቦክ ዛሬ አውስትራሊያ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በገዢው ፓርቲ ላይ «APT28» በተባለ የሩስያ ጸረ ሳይበር ቡድን ከተቃጣው  ጥቃት ጀርባ የሩስያ መንግስት መኖሩን ማናገር እንችላለን» ማለታቸውን አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።

 ለውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ  ጠንከር ያለ ክስ ከወደ ሩስያ ለጊዜው የተሰማ ነገር የለም።

ቤርቦክ ቻይና በፓስፊክ ክልል ተጽዕኖ እያሳደረች መምጣቷን ተከትሎ ከአውስትራሊያ ፣ ኒውዚላንድ እና ፊጂ ደሴቶች ጋር በጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የነበራቸውን የትብብር ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በሶስቱ ሃገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ጀርመን በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ሁለት ዓመታትን በተሻገረው ጦርነት  ዘመናዊዎቹን የሊዮፓርድ ታንክ እና ፓትሪዮት የአየር መከላከያ ስረዓት ጨምሮ የቢሊዮን ዶላሮች ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን በመስጠቷ ከሩስያ ብርቱ ወቀሳ እና ውግዘት ሲደርስባት ቆይቷል።

 

የቀድሞው የሩሲያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት ዩልያ ናቫልኒ የ2024 የዶቼ ቬለ የመናገር ነጻነት ሽልማትን አሸነፉ።

ባለቤታቸውን በሩስያ በእስር ቤት  በድንገት በሞት የተነጠቁት ዩሊያ ሃሳባቸውን ለመግለጽ «የማይናወጥ አቋም » መያዛቸው ለሽልማት እንዳበቃቸው የዶይቼ ቬለ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር ሊምቡርግ ተናግረዋል። 
ዩሊያ ናቫልኒ የባለቤታቸው አሌክሲ ናቫልኒ ህልፈት ከተሰማ በኋላ በአውሮጳ ህብረት የህግ አውችዎች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር    ባለቤታቸው በሩስያ መንግስት መገደላቸውን በይፋ ተናግረዋል።
« ፑቲን ባለቤቴ አሌኪሲ ናቫልኒን ገድሎታል፤ በእርሱ ትዕዛዝ ለሶስት ዓመታት አሌክሲ ላይ አካላዊ ጥቃት ደርሶበታል፤ እጅግ ጠባብ በሆነ ክፍል ውስጥ አስረው በስልክም ሆነ በደብዳቤ እንዳይገናኘኝ አድርገው ከተቀረው ዓለም እንዲገለል አድርገውታል ። ከዚያም ገደሉት ። »
ዩሊያ  በተለይ ከባለቤታቸው ህልፈት በኋላ በሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ግንባር ቀደም የተቃዉሞ ድምጽ መሆን ችለዋል። በዚህም ጀርመን ውስጥ በቅርቡ በተመሳሳይ የመናገር ነጻነት ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል። የጀርመን ዓለማቀፍ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዶቼ ቬሌ በየዓመቱ በመናገር ነጻነት አሸናፊ የሆኑትን ሲሸልም ቆይቷል። በጎርጎርሳውያኑ 2023 ኤልሳልባዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ የመናገር ነጻነት አሸናፊ ነበር። 
ዩሊያ ናቫልኒ ግንቦት ወር መጨረሻ በሪሊን ውስጥ በሚከናወን ይፋዊ ስነስረዓት ሽልማታቸውን እንደሚቀበሉ ሲጠበቅ ፤ ሽልማቱ  10ኛው የመናገር ነጻነት ሽልማታቸው ይሆናል ።

ቱርክ በጋዛ ሰርጥ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረስ  ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ማቋረጧን ዛሬ አስታወቀች። በጋዛ የሰብአዊ እርዳታ ሊረጋገጥ ይገባልም ብላለች ። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ «ተቀባይነት የሌለው» ያሉትን በራፋህ አካባቢ ልትፈጽም የተዘጋጀችው ውጊያ ቱርክ የወች እና ገቢ የንግድ ግንኙነቷን እንድታቋርጥ አስገድዷታል ሲሉ የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ኦሜር ቦላት ተናግረዋል። የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ካትዝ የቱርኩን ፕሬዚዳንት እርምጃ ዓለማቀፍ የንግድ ስምምነቶችን የሚጥስ ሲሉ ነቅፈውታል። የፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ በበኩሉ «ለፍልስጥኤማውያን መብት የቆመ» ሲል የቱርክን እርምጃ አሞካሽቷል። ቱርክ ወደ እስራኤል ከባድ ማሺኖችን ጨምሮ ብረታ ብረስ ፣ ተሽከርካሪዎች፣ የፕላስቲክ ውጤቶች እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን ስትልክ ፤ በአንጻሩ ከእስራኤል ነዳጅ ታስገባለች።

ሁለቱ ሃገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጣቸው 7 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።

 

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።