1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የጥገኝነት አሳጣጥ ፖሊሲ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 6 2015

የኅብረቱን እቅዶች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ክፉኛ ተችተዋል።የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ማሻሻያው ስደተኞችን የሚገፋ ነው በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው። ውሳኔው «ለኛ በማንኛውም መለኪያ ታሪካዊ ስህተት ነው።»ያሉት ለስደተኞች መብት የቆመው ፕሮ አዙል የተባለው ድርጅት የአውሮጳ ኅብረት ጉዳዮች ሃላፊ ውሉን ሃላፊነትን ወደ ጎን የተወ ብለውታል።

https://p.dw.com/p/4SX7L
Luxemburg Innenministertreffen der EU
ምስል Alexandros Michailidis/European Council/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ፣ከብዙ አሥርት ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ የኅብረቱን የፍልሰትና የጥገኝነት አሳጣጥ ፖሊሲ ለማሻሻል ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሉክስምበርግ ውስጥ በጉዳዩ ላይ የተነጋገሩት የኅብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች  ስደተኞችን በፍትሀዊነት ለመከፋፈል ፣ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን በፍጥነት ወደመጡበት መመለስ እንዲችሉ የጥገኝነት ማመልከቻዎችን የሚያስተናግዱበትን አሰራር ለመለወጥ አቅደዋል። ተዘዋዋሪውን የአውሮጳ ኅብረት የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዘችው የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የስዊድን የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ስምምነቱ እውን መሆኑን ማመን እንዳቃታቸው ነበር የተናገሩት።ሚኒስትሯ ማርያ ማልመር ስቴነግራድ በመሩት 12 ሰዓታት በፈጀው ውይይት የተደረሰበት ይሆናል ብለው ያልጠበቁት ያለፈው ሳምንቱ ስምምነት በጣም አስደስቷቸዋል። የተስማሙባቸውን የሁለቱን ሰነዶች ምንነትም ገልጸዋል። 
«እውነት ለመናገር እዚህ ተቀምጬ ይህን እናገራለሁ ብዬ አላምንም ነበር።ሆኖም ይኽው እዚህ ደርሰናል።የኅብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጥገኝነትና በፍልሰት አስተዳደር ደንብ እንዲሁም በተገን አሰጣጥ ሂደት ደንብ ላይ አጠቃላይ አሰራሮችን በማጽደቃቸው ከመጠን ያለፈ ተደስቻለው፤ይህን በማሳወቄም ኮርቻለሁ። እነዚህ ሁለት ሰነዶች ፣ የአውሮጳ ኅብረት የተገን አሰጣጥ ስርዓት ማሻሻያ ሁለት ዋነኛ ዓምዶችን እንዲሁም ሃላፊነትና ትብብርን በጥሩ ሁኔታ የሚያመጣጥን ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ሰነዶች ፍልሰትን የሚያስተዳድረው እና በአመዛኙ የአውሮጳውያንን እሴቶችና የዓለም አቀፍ ሕግን ሙሉ በሙሉ መሠረት ያደረጉ አንድ የጋራ የአውሮጳ የፍልሰት ፖሊሲ ማዕከላዊ ክፍሎች ናቸው። » 
ሚኒስትሯ ስምምነቱን ታሪካዊና ብዙ ነገሮችን የሚያመለክትም ሲሉ ነበር ያወደሱት።
«በስተመጨረሻ በርካታ አባል ሀገራትን በጋራው አቋም ላይ አንድ እንዲሆኑ ማድረግ መቻል ታሪካዊ እርምጃና ትልቅ ስኬት ነው።የአውሮጳ ማኅበረሰብ በጋራ በመስራት፣በፍልሰት ጉዳይ ላይ ታላላቅ ነገሮችን ማሳካት እንደሚችል ዳግም አሳይተናል።»
በአውሮጳ ኅብረት የሚገኙ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን አባል አገራት እንዴት  ይከፋፈሉ የሚለው ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት አከራክሯል። አብዛኛዎቹ ኅብረቱ ሕገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞች አውሮጳ የሚገቡት ጣልያን ግሪክና ስፓኝን በመሳሰሉ በኅብረቱ ደቡባዊ የባህር ዳርቻዎች በኩል ነው። ስደተኞቹ ከሊቢያ ከቱኒዝያ ከሞሮኮ ወይም ከቱርክ በለንቋሳ ጀልባዎች ተጭነው በአደገኛ የባህር ጉዞ ነው ወደነዚህ ሀገራት የሚሄዱት።እስካሁን በሚሰራበት የአውሮጳ ኅብረት ሕግ መሠረት  ስደተኞች ተገን መጠየቅ ያለባቸው መጀመሪያ በገቡበት ሀገር ነው።ይህም በተለይ የአውሮጳ ኅብረት ደቡባዊ ድንበር የሆኑት ጣልያን ግሪክና ስፓኝከፍተኛ ጫና አድሮብናል ሲሉ ከኅብረቱ ተጨማሪ  እርዳታ እንዲጠይቁ አድርጎላቸዋል። ይሁንና ከተወሰኑ የኅብረቱ አባል ሀገራት ውጭ ስደተኞችን ለመከፋፈል ፈቃደኛ የሆኑ ሀገራት ብዙም አልነበሩም።በተለይ የሰሜንና ምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት የህዝባቸው ብዛት እየታየ የተወሰነባቸውን ስደተኞች እንዲወስዱ ለማስገደድ፣ ኅብረቱ ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁንና ጥረቱ አልተሳካም።የፍልሰት ጉዳዮች አዋቂ ሄሌና ሀን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ይህን መሰሉ የግዳጅ አሰራር መቼም ቢሆን  ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።
« በጊዜ ሂደት የእምነት መሸርርሸር አጋጥሞ አይተናል። ለምሳሌ በኅብረቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ አባል ሀገራት ከሌሎች አባል ሀገራት  ማግኘት የሚፈልጉትን ድጋፍ አላገኘንም የሚል ስሜት አድሮባቸዋል። ሆኖም በስደተኞች ቁጥር መጨመር የተነሳ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎችና ህዝበኛ ፓርቲዎች በአንዳንድ አባል ሀገራት አብላጫ ድምጽ ሲያገኙ አይተናል።ወደ ቀኝ የማዘንበል አዝማሚያ ተመልክተናል። በዚህ የተነሳም ከቀድሞው የጠነከረ ገደብ የያዙ የፍልሰት ፖሊሲዎችም ተበራክተዋል።» 
በአዲሱ ስምምነት መሠረት አባል ሀገራት በአንድ ስደተኛ 20 ሺህ ዩሮ ወይም 21 ሺህ 553 ዶላር ከከፈሉ ስደተኞችን ለመውሰድ አይገደዱም።ገንዘቡም በብራሰልስ በሚተዳደር የባንክ ሂሳብ ውስጥ ይቀመጣል ተብሏል። ሀን እንዳስረዱት ስምምነቱ አባል ሀገራት በስደተኞች ለተጨናነቁት ሀገራት ኅብረታቸውን ለመግለጽ  ይህን አማራጭ አስቀምጦላቸዋል። 
«አባል ሀገራት ስደተኞችን በግዴታ እንዲወስዱ የቀረበ አማራጭ አልነበረም።ይህ የሆነበት ምክንያትም በፖለቲካዊ መንገድ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ስለሆነ ነው። የተነጋገሩት  በግዴታ ስለሚደረግ ትብብር ነው። ሀሳቡ ምንድን ነው አባል ሀገራት በስደተኞች ለተጨናነቁት ሀገራት ኅብረታቸውን ለመግለጽ ይህኛው አማራጭ ተቀምጦላቸዋል። በአንድ በኩል ከጎርጎሮሳዊው 2015ና 2016 በኋላ እንደነበረው ስደተኞችን ወደ ሌላ ሀገር መውሰድ ይኖራል።በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁም የቁሳቁስ እርዳታም የማድረግ አማራጭ አለ ።  »  
ይሁንና አንዳንድ የኅብረቱ አባል ሀገራት በእቅዱ አልተሰማሙም። ፖላንድና ሀንጋሪ የቀረቡትን አማራጭ መፍትሄዎች  የተቃውመው ነው ድምጻቸውን የሰጡት ። ቡልጋሪያ ማልታ ሊትዌንያ እና ስሎቫክያ  ድምጻቸውን አቅበዋል።የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በማግስቱ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት ስምምነቱ «ተቀባይነት የለውም» ብለዋል። «እነርሱ» የተቀሩትን የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ማለታቸው ነው ሀንጋሪ በግዳጅ ወደ ፍልሰተኞች ሀገር እንድትቀየር ነው የሚፈልጉት ሲሉም ቁጣቸውን ገልጸዋል። ፖላንድም እንዲሁ ቅሬታዋን አሰምታለች። ይሁንና የሁለቱ ሀገራት ተቃውሞ በብዙሀኑ አባላት እሺታ ተሸንፎ ስምምነቱ አልፏል። 
ሚኒስትሮቹ ከዚህ ሌላ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተገን የማግኘት እድላቸውን መሠረት አድርገው የሚለዩበት አዲስ የአሰራር ስልት ላይም ተስማምተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2022 በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ከጠየቁት መካከል 40 በመቶው ብቻ ናቸው ተቀባይነት ያገኙት።ባለሥልጣናት አሁን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎችን አጣድፈው ወደ መጡበት መመለሱ እንዲፋጠን ይፈልጋሉ። በእቅዱ መሠረት የተሻለ ደኅንነት አላቸው ከሚባሉ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ማመልከቻዎችን ድንበር ላይ በፍጥነት ለማየት ታስቧል። ከነዚህ ውስጥ ከህንድ ከሰሜን መቄዶንያ ከሞልዶቫ ከቭየትናም ከቱኒዝያ ቦስንያ ሄርዞጎቪና ሰርቢያ እና ኔፓል የመጡ  እውቅና ያላገኙ ከ20 በመቶ በታች የሆኑ አመልካቾች ይገኙበታል። ስደተኞችን መጠረዙ ብሔራዊ የፀጥታ ስጋት የሚባሉትንም ይጨምራል። እነዚህ አዲሱ ስደተኞች በአውሮጳ የሚስተናገዱበት የተባለ አሰራር  የሚመለከታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ወደ አውሮጳ ሀገራት እንዳይገቡ አግደው ድንበር ላይ በሚዘጋጁ ልዩ ማዕከላት ለማቆየት ነው የታቀደው። እነዚህን የኅብረቱን እቅዶች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ክፉኛ ተችተዋል። የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማሻሻያው በተለያዩ ምክንያቶች ስደተኞችን የሚገፋ ነው በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው። በብሪታንያው ግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም የፍልሰት ጉዳዮች አዋቂ ስቴፋን ፖፕ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትን ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሲሉ ኮንነዋቸዋል።  ውሳኔው «ለኛ በማንኛውም መለኪያ ታሪካዊ ስህተት ነው።»ያሉት ለስደተኞች መብት የቆመው ፕሮ አዙል የተባለው የጀርመን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የአውሮጳ ኅብረት ጉዳዮች ሃላፊ ካርል ኮፕ የኅብረቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተስማማበትን ውል ሃላፊነትን ወደ ጎን የተወ ሲሉ ነው የገለጹት   
«ትናንት የተላለፈው ውሳኔ  በርግጥም ፈቃደኛ ያልሆኑት ኅብረት የጥገኝነት ማሻሻያ እንለዋለን ።ግን እውነታው ስደተኞች ከሌላ ፣ከአውሮጳ ውጭ ከሆነ ሦስተኛ አገር ጥበቃ የሚያገኙበትን መንገድ ከውጭ እንፈልጋለን ነው።ይህ ለዓለም በጣም መጥፎ ምልክት ነው። የ27 ዴሞክራሲያዊ ሀገራት ትልቅ ክለብ ፣’’አዎ ስደተኞች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፤እባካችሁ እዚህ ግን አይደለም‘‘ ይላል።ይህ እንግዲህ ለሌሎች በዓለማችን ለሚገኙ አካባቢዎች መጥፎ አርአያ ይሆናል።» 
የአውሮጳ ኅብረት የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ኢልቫ ጆሀንሰን ግን አዲሱን ስምምነት፣ የተገን አሰጣጥ ሂደትን የሚያቀላጥፍ ተገን ጠያቂዎችንም ከመንገላታት የሚያድን አሰራር ነው ሲሉ ይሞግታሉ።  
«ይህ ፈጣን ሂደቶችና ፈጣን የመመለስ ውሳኔዎችን ለማግኘት ግልጽ አማራጭ ነው። ይህ ከአውሮጳ ወደ መጣበት ለሚመለሰው ስደተኛ መጠን እንዲሁም ለረዥም ጊዜ እጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን ሳያውቁ ለሚቀመጡ ተገን ጠያቂዎችም አስፈላጊ ነው።በአውሮፓኅብረትለአራትና ከዚያም በላይ ዓመታት የቆዩ ስደተኞችን ስንመልስ በርግጥ መመለሱ ለነርሱ ከባድ ውሳኔ ነው።እናም ፈጣኑ አሰራር ፈጣን ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይበልጥ ሰብዓዊ ነው።»
በውሉ መሠረት ደኅነንታቸው ዝቅ ያለ ከሚባሉ ሀገራት ማለትም ከሶሪያ ከቤላሩስ ከኤርትራ ከየመንና ከሶማሊያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እውቅና የሚያገኙ ስደተኞች   ጉዳይ በተለመደው የተገን አሰጣጥ ስርዓት ይስተናገዳል ተብሏል።ያም ሆኖ የፕሮ አዙሉ ካርል ኮፕ ግን የኅብረቱ አባል ሀገራት በተስማሙበት ውል ፍትሀዊ የጥገኝነት አሰጣጥ ሂደት ሊኖር አይችልም ይላሉ።
«አሁን እንደምናውቃቸው እንደ አግያን ባህሩ ኅብረቱ በገንዘብ የሚደግፋቸው ቁጥጥር የሚደረግባቸው የስደተኞች መጠለያዎች በአውሮጳ ኅብረት  የውጭ ድንበሮች ይመሰረታሉ።አውሮጳ በሺህዎች የሚቆጠሩ እስር ቤት መሳይ መጠለያዎችን ለተገን ጠያቂዎች ማስተናገጃነት መጠቀም ይፈለጋል። እኛ በእስር ቤት መሰል ሁኔታዎች ውስጥ ፍትሀዊ የጥገኝነት አሰጣጥ ሂደት አይኖርም ነው የምንለው።  ህጻናትን የማሰርም አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አይቻልም።»
ምንም እንኳን የአውሮጳ ኅብረት ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት የተስማሙበትን ውል ታሪካዊ ብለው ቢያወድሱትም ሂደቱ ግን በዚህ አላበቃም። የአባል ሀገራት የህዝብ ተወካዮች ምርክር ቤት አባላት ገና አስተያየት ይሰጡበታል። ምናልባትም ከድርድሮቹ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የመጨረሻው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።ኅብረቱ ድርድሩ ያን ያህል ከባድ ይሆናል ብሎ አያስብም። ካርል ኮፕ የኅብረቱ ምክር ቤት አባላት በዚህ ጊዜ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።  ለሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች የመቆም እና መጥፎ ያሉትን ይህን ስምምነት ማሻሻል የነርሱ ድርሻ እንደሆነም አሳስበዋል።  

Luxemburg Innenministertreffen der EU | Nancy Faeser
ምስል Alexandros Michailidis/European Council/dpa/picture alliance
Luxembourg EU-Minister Migrationsabkommen
ምስል RTRTV
Luxemburg Innenministertreffen der EU | Maria Malmer Stenergard
ምስል Alexandros Michailidis/European Council/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ታምራ ዲንሳ