1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሰቆቃ በሳዑዲ እስር ቤቶች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 12 2015

ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት በጎደለው እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ታስረው ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4LHCW
Äthiopische Rückkehrer aus Saudi-Arabien
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከ ሳዑዲ አረቢያ ወደ አትዮጵያ ሲመለሱ ምስል Solomon Muchi/DW

በ“አስከፊ”ና “ኢ-ሰብዓዊ” አያያዝ እስር ላይ ይገኛሉ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል አርብ ታኅሣሥ 7፤ 2015 ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት በጎደለው እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ታስረው ይገኛሉ ብሏል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪቃ ቀጠና ዳይሬክተር ሔባ ሞራዬፍ፤ ሳዑዲ አረቢያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ እያሰረች እና በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሰች እንደምትገኝ አስታውሰዋል።“በአሁኑ ወቅት ከ30,000 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን“አስከፊ” እና “ኢ-ሰብዓዊ” መንገድ  በእስር ላይ ይገኛሉ ያሉት ሔባ ሞራዬፍ የስደተኞቹ  የአስተሳሰር  ሁኔታ “የረዥም ጊዜ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት”ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል። 

ከአንድ ወር በፊት ሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ውስጥ ከሚገኘው ካብ እስር ቤት ከአንድ ዓመት እስር በኋላ ተለቆ ወደ አገሩ የገባው  ሀዱሽ ሙሾ እስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ መሆኑን እና በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንደሚገኙ እንዲ ሲል ገልጿል።

«ጅዳና ሪያድ ነው ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ታስረው የሚገኙት። እኔ እራሴ ወጥቼ ድምፅ እሆናለሁ ብዬ ነበር ግን በምን አቅሜ። በጣም አሳዛኝ ነው ስለሚራቡ ታማሚ አለ። በጣም ኃይለኛ ረሐብ ነው ያለው ። የሚሰጠው ቁርስም ሆነ እራት ተመጣጣኝ አይደለም። በርካታ ሆነን ስለታሰርን አየር የለም። ሰውነቴ ሁላ ቆስሎ ነው የወጣውት። በጣም ታመህ ታምሚያለው ብለህ ህክምና አታገኝም። ላለው ታሳሪ ህክምናውም አይበቃም። ትንሽ ትንሽ ህክምና ነው ያለው እሱም አይበቃም። ከ100 ሺ በላይ እስረኛ ነው ያለው እዛው»

በሳዑዲ አረቢያ በሰው ቤት ተቀጥራ የምትሠራው እና ወንድሟ በሪያድ ከተማ በሚገኘኝ እስር ቤት ውስጥ ከታሰረ አምስት ወር እንዳለፈ የተናገረችው ወጣት አዚዛ ወንድሟ አመቺ ሰአት ሲያገኝ ስልክ እንደሚደውልላት እና ያለውን ነገር እንደሚነግራት እንዲ ስትል ተናግራለች። 

Äthiopien | Rückkehrer aus Saudi-Arabien
ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ አረቢያ ሲመለሱምስል Solomon Muche/DW

«በኢትዮጵያ ከቀኑ ስድስት ሰአት ተደዋውለን ነበረ ስልክ እንደፈለጉ አያገኙም። ያሉበት በጣም ከባድ እንደሆነ እና ምግብ እንደማይጠግቡ እንዲሁም አየር ማቀዝቀዣ ክፍት በመሆኑ በጣም እየበረዳቸው እንደሆነ ነገር ግን በጣም የበዛው ረሐብ እንደሆነ እና ለረሐብ ማስታገሻ  ብስኩት በጥብጦ እንደሚጠጣ ነግሮኛል። ለኛ ለኢትዮጵያውያን ደንታ እንደሌላቸው እና ለኛ ለኢትዮጵያውያን ለየት ያለ ጥላቻ እንዳላቸው ነው ነው የሚነግረኝ ግን ከምንም በላይ ረሐቡ ከባድ ነው በተለይ ለወንድ ልጅ።»

አምነስቲን ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስለሚደርስባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ በሪያድ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለተከታታይ ሦስት  ቀናት  በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ግን ሐሳባቸውን ልናካትት አልቻልንም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሚያዝያ 2013 እስከ ግንቦት 2014 ባለው ጊዜ በሁለት እስር ቤቶች ውስጥ 10 ኢትዮጵያውያን እስረኞች አብዛኞቹ አንገብጋቢ የመድኃኒት አቅርቦት በመነፈጋቸው እንዲሁም አንድ እስረኛ በደረሰበት ድብደባ መሞታቸውን ገልጿል። ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልሰተኛ ሠራተኞች እንደሚገኙ የአምነስቲ ዘገባ ይጠቁማል። 

ማኅሌት ፋሲል 
ማንተጋፍቶት ስለሺ