1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የቅድመ ታሪክ የቡና መገኛ መሆኗን አዲስ የዘረመል ጥናት አረጋገጠ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

አዲሱ ጥናት እንዳረጋገጠው አረቢካ የቡና ዝርያ የተገኘው ከ610,000 እስከ አንድ ሚሊዮን ዓመታት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ደኖች ውስጥ ነው። ይህ የቡና ዝርያ ከዛሬ 300,000 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ከነበረው ዘመናዊ የሰው ዝርያ /Homo sapiens/ በዕድሜ ቀደምት ነው።

https://p.dw.com/p/4f6BX
የኢትዮጵያን የቡና
የኢትዮጵያን የቡና ምስል Seyoum Getu/DW

አዲስ የዘረመል ጥናት በኢትዮጵያ ቡና ላይ


የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በቡናን ቅድመ ታሪክ አመጣጥ ላይ ሰፊ ትንታኔ ባቀረበ እና ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር መሆኗን ባረጋገጠ አዲስ የዘረመል ጥናት ላይ ያተኮረ ነው።
ቡና በዓለም ላይ ተወዳጅ ከሆኑ መጠጦች አንዱ ሲሆን፤መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ  ከ2.25 ቢሊዮን በላይ ሲኒ በየቀኑ ይጠጣል።
በኒዮርክ የቡፋሎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በቅርቡ ይፋ ባደረጉት  አንድ  ጥናት በዚህ ተወዳጅ መጠጥ ቅድመ ታሪክ ላይ ዘርዘር ያለ መረጃ አውጥተዋል።በኔቸር ጄኔቲክስ መፅሄት ላይ በቅርቡ ታትሞ የወጣው ይህ ጥናት  ከዓለም የቡና ምርት  60%  ይይዛል ተብሎ በሚገመተው በአረቢካ ቡና ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በዚህ የቡና ዝርያ የዘረመል ታሪክ ላይ ጥልቅ ትንተና ተደርጓል።
በብዙ የዜና አውታሮች ሰፊ ሽፋን ያገኘው ይህ አዲስ ጥናት የአረቢካ የቡና ዝርያ በጊዜ እና በመልከዓምድር  የነበረውን አስደናቂ  ጉዞ እና ዝግመተ ለውጥም በስፋት ቃኝቷል። 
ተመራማሪዎች በአዲሱ ጥናት ባደረጉት የዘረ-መል  ትንተናም፣ የአረቢካ ቡናን የዝግመተ ለውጥ አካሄድን በተመለከተ፣ የት እንደተገኘ  እና በሺህ ዓመታት ውስጥ እንዴት እንደተላመደ ሰፊ መረጃ  ሰጥተዋል። 
መነሻው ከኢትዮጵያ መሆኑ የሚነገርለት በሳይስሳዊ ስሙ የአረቢካ ቡና /Coffea Arabica- / በጣዕሙ በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ ቡና ነው። ይሁን እንጂ፤ ድርቅ እና በሽታን የመቋቋም አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ለቡና አምራች ገበሬዎች ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ስጋት በስዊዘር ላንድ የቤርን ዩንቨርሲቲ የዕፅዋት ሳይንስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ እንደሚሉት አዲሱ ጥናት ይህንን ችግር የሚፈታ ይመስላል።

ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ ፤ በስዊዘርላንድ የቤርን ዩንቨርሲቱ ከፍተኛ የዕፅዋት ተመራማሪ
ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ ፤ በስዊዘርላንድ የቤርን ዩንቨርሲቱ ከፍተኛ የዕፅዋት ተመራማሪምስል Privat

ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና መገኛ ሀገር

አረቢካ ቡና ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ሲመረት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ ቢሆንም፤ አዲሱ ጥናት እንዳረጋገጠው ይህ  የቡና ዝርያ የተገኘው ከ610,000 እስከ አንድ ሚሊዮን ዓመታት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ደኖች  ውስጥ ነው። ይህ የቡና ዝርያ ከዛሬ 300,000 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ከተነሳው ዘመናዊ የሰው ዝርያ /Homo sapiens/ በዕድሜ ቀደምት ነው።“የቡና መገኛ ስፍራ”ን የማልማት ጥያቄ
እንደ ጥናቱ ከዚህ በፊት ይታመን ከነበረው መላ ምት በተቃራኒ የአረቢካ ቡና ሰዎች ያበቀሉት እና በሰው ጣልቃገብነት የተገኘ ሳይሆን ሲንፎራ /Coffea canephora/ እና ዩጂኖዮድስ /Coffea eugenoides/ከተባሉ ሁለት የቡና ዝርያዎች በተፈጥሮ የተዳቀለ ሆኖ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ቡና
ጮጬ (ከታ ሙዱጋ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የቡና መገኛ ነው ተብሎ በሽማግሌዎች የሚታመንበት ቦታ ምስል Seyoum Getu/DW

የጥናቱ ዋናዋና ግኝቶች 

ጥናቱ እንደሚያሳየው የአረቢካ የጉዞ ፍሰት በሺህ ለሚቆጠሩ አመታት በተከሰተው የአየር ንብረት መለዋወጥ  የተቀረፀ ነው። የጥናት ቡድኑ አባል ፕሮፌሰር አልበርት እንዳሉት ይህ ጥንታዊ የቡና ዝርያ  ከኢትዮጵያ  ወደ የመን ከዚያም ወደ ህንድ በመጨረሻ  ወደ መላው ዓለም ተሻግሮ በስፋት ከመመረቱ  በፊት የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦችን አሳልፏል።
ይሁን እንጅ ዝቅተኛ የዘረመል ብዝሃነት ስላለው የአረቢካ ቡና ዝርያ ለተባይ እና ለበሽታ የተጋለጠ እና ምርቱም ተስማሚ የአየር ንብረት ባሉባቸው አካባቢዎች ብቻ የተገደበ ነው።
ተመራማሪዎቹ የዚህን የቡና ዝርያ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዘረ መል ለመፍጠር  ካርል ሊኒየስ የተጠቀሙበትን የ18ኛው ክፍለ ዘመን ናሙናን ጨምሮ የ 39  የአረቢካ ቡና ዝርያዎችን የዘረ-መል መረጃን ቅደም ተከተል የማስያዝ ስራ ሰርተዋል። በዚህም በሽታን ለመቋቋም ወሳኝ የሆነውን የተወሰነ የዘረ-መል መረጃ / የጂኖም/ክፍል ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።ይህም እንደ ፕሮፌሰር ዘሪሁን የጥናቱ ዋና ግኝት ነው።

የጥናቴ ጠቀሜታ ለኢትዮጵያውያን የቡና ተመራማሪዎች እና ገበሬዎች 

ጮጬ (ከታ ሙዱጋ)፤ በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የቡና መገኛ ነው ተብሎ በሽማግሌዎች የሚነገርለት ቦታ
በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው በጅማ የቡና መገኛ ነው የሚባልለት ጮጬ (ከታ ሙዱጋ) ከጅማ ከተማ 45 ኪ.ሜ ገደማ ላይ ከምትገኘው አጋሮ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ስፍራ የአረቢካ ቡና መገኛ ነው በሚል በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ይነገራልምስል Seyoum Getu/DW

ከዚህ አንፃር በአዲሱ የዘረመል ምርምር፤  የአረቢካ ቡና አመጣጥ ቅድመ ታሪክ ከመተንተን ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እና የዚህን የቡና ዝርያ የወደፊት ህልውና የሚያረጋግጡ ዝርያዎችን ለማዘጋጀት መሠረት የሚጥል ነውም ተብሏል። 
የጥናቱ ተባባሪ ፀሀፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ቪክቶር አልበርት ለሮይተርስ የዜና ምንጭ እንደገለፁት ፤አሁን ካሉ እፅዋት የዘረ-መል መረጃን  በመውሰድ፤ የአረቢካ ቡናን ረጅም ታሪክ እና ትክክለኛ ምስል ወደ ኋላ ተመልሰው ለማሳየት ተመራማሪዎቹ የሚቻለውን ሁሉ አድርገዋል።በጥናቱ ከ12 ሀገራት 40 መስሪያ ቤቶች  እና 69 አጥንዎች ተሳትፈውበታል።ነገር ግን አንድም ኢትዮጵያዊ በጥናቱ አለመሳተፉን ፕሮፌሰር ዘሪሁን በቁጭት ያነሳሉ። 
ያም ሆኖ የጥናቱ ግኝቶች ለቡና አምራች ገበሬዎች ፈታኝ ሆኖ የቆየውን ችግር በመፍታት ረገድ ለኢትዮጵያውያን የቡና ተመራማሪዎች እና አምራቾች ተስፋ የሚሰጥ ነው ይላሉ። 
በአዲሱ ጥናት የተገኙ ውጤቶችን መሰረት በማድረግም ኢትዮጵያውያን የቡና ተመራማሪዎች ቀጣይ ምርምሮችን ለመስራት እና ቴክኖሎጅውን ለማሸጋገር እንደሚችሉም ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ ፤ በስዊዘርላንድ የቤርን ዩንቨርሲቱ ከፍተኛ የዕፅዋት ተመራማሪ
ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታደለ ፤ በስዊዘርላንድ የቤርን ዩንቨርሲቱ ከፍተኛ የዕፅዋት ተመራማሪምስል Privat

ዘረ መል የማሻሻል ሂደት 

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ፤የአየር ንብረት ለውጥ  ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚችሉ ጠንካራ ዝርያዎችን ለማዳበር የአረቢካን የዘረመል ታሪክ መረዳት ወሳኝ ነው። ከዚህ አንፃር  የመጀመሪያውን ተፈጥሯዊ የመዳቀል ክስተትን ጨምሮ በአረቢካ የዝግመተ ለውጥ ታሪክ ውስጥ ጉልህ የሆኑ ክስተቶችን በጥናቱ አመልክተዋል።በደን ምንጣሮ የሚመረተውን ምርት ያገደው የአውሮፓ ህግ እና ስጋቱ
በጥናቱ አጠቃላይ  ትንተና የአረቢካን በሽታ የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ ተስፋ ሰጭ መንገዶችን አመላክቷል። ጥናቱ ከበሽታ መቋቋም ጋር የተዛመዱ የዘረመል ክፍሎችን በመለየት እና በማሻሻል /Gene Editing/ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ተስፋ አሳድሯል።ለመሆኑ ዘረ መል የማሻሻል /Gene Editing/ ማለት ምን ማለት ነው?ፕሮፌሰር ዘሩሁን።
ለመሆኑ በአራቢካ ቡና የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ የሚደረገው ዘረመል የማሻሻል ሂደት በቡናው ጣዕም እና የንጥረ ነገር ይዘት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን?

የተቆላ የኢትዮጵያ ቡና
የተቆላ የኢትዮጵያ ቡና ምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ቡና ተጨማሪ እውነታዎች

በዓለም ላይ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት አረቢካ /Coffea arabica/ እና ሮቡስታ /Coffea robusta/የተባሉት ሁለት ዋና ዋና የቡና ዝርያዎች ሲሆኑ፤ ከዓለም የቡና ምርት ውስጥ ከሁለት በመቶ በታች የሚሆነው ሶስተኛው የቡና ዝርያ ደግሞ ላይቤሪካ የሚባለው ነው። ላይቤሪካ ቡና/Coffea Liberica/ ከምዕራብ አፍሪቃ በተለይም ከላይቤሪያ ሴራሊዮን በጎርጎሪያኑ 1872  የተገኘ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
መነሻው ከኢትዮጵያ የሆነው የአረቢካ ቡና በዓለም ላይ ከ60 በመቶ በላይ ጥቅም ላይ የሚውል በጣዕሙ ተወዳጅ የቡና ዝርያ ሲሆን፤ የሚመረተው በከፍተኛ ቦታዎች ነው። ሮቡስታ ደግሞ በሞቃታማ የአየር ጠባይ ለባህር ጠለል ቅርብ በሆነ አካባቢዎች ይመረታል።ይህ የቡና ዝርያ በጣዕሙ መራራ ሲሆን፤ በውስጡ ያለው የአነቃቂ ንጥረ ነገር/የካፌይን/ ይዘቱም ከፍተኛ ነው።  

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ